የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አጭር ገፅታ

ሀገራችን በ2000 ዓ.ም በቤጂንግ ኦሎምፒክ በሁለት አትሌቶች ብቻ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኝቷ ሀገራችን የነበራትን አኩሪ ውጤት ጥያቄ ውስጥ በማስገባቱ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተተኪ አትሌቶችን በብዛት እና በጥራት በማፍራት የእኛነታችን መገለጫ የሆነው የአትሌቲክሱን ውጤት በዘላቂነት ለማስቀጠል የማዕከላት ግንባት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ሆኖ በመገኙቱ በ2002 ዓ.ም አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ጥረት ሊቋቋም ችሏል፡፡

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በኦሮሚያ ክልል በአሰላ ከተማ በጥቅምት 2002 ዓ.ም 250 አትሌቶችን ከሁሉም የሀገሪቷ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በተዘጋጀው የመመልመያ መስፈርት መሠረት በመምረጥና በ21 አሰልጣኞች በሶስቱ የአትሌቲክስ ዘርፎች በ(ሩጫ፣በውርወራ እና በዝላይ) ስልጠና ጀመረ፡፡

እንዲሁም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በሴቶች እና ወንዶች የእግር ኳስ ስልጠናን በማካተት ዘመናዊና ሳይንሳዊ ስልጠና በመስጠት በሀገር ውስጥ፣ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እና ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማስገኘት ባለፈ የሀገራችንን ገጽታ በአለም መድረክ ለማሳወቅ የበኩሉን ጥረት አድርጓል አሁንም እያደረገ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የሀገራቸንን ሰንደቅ በተለያዩ የስፖርት ውድድር መድረኮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት የቻሉ የስፖርት አምባሳደሮችን በተለይም በአትሌቲክሱ ዘርፍ እንደነ ኃይለማርያም አማረ፣ ጅክሳ ቶሎሳ፣ ወይንሽት አንሳ፣ ተስፋዬ ዲሪባ፣ ዘገየ ሞጋ፣ ኡቶ ኡኬሎ፣ አርያት ዲቦ ፣ሊንጎ ኡባንግ፣ ለሜቻ ግርማ፣ ኡመድ ኡኩኝ፣ ኤቢሴ ከበደ፣ መርሃዊት ፀሐዬ፣ ኤቢሴ ከበደ፣ ዝናሽ ተስፋዬ፣ ደረሰ ተስፋዬ፣ ዝናሽ አሰፋ፣ ኡቴጌ ኡባንግና የመሳሰሉትን እንዲሁም በእግር ኳስ ሴናፍ ዋቁማ፣ እምወድሽ ይርጋሸዋ፣ ትደግ ፍሰሀ፣ ናርዶስ ጌትነት፣ ዮዲትና ቤካ አብደላን  የመሳሰሉ ታዳጊዎች ማፍራት ችሏል፡፡

የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በሀገሪቱ የተተኪ ስፖርተኞችን እጥረት ለመቅረፍና በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የሚኒስትሮች ም/ቤት በደንቡ ቁጥር 294/2003 የተቋቋመ የስልጠና ማዕከል ነው፡፡

      

ይህ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በህግ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አኳያ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች በመመልመል በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በማሰልጠን ለሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ውድድሮች በአካለዊ፣ አእምሮአዊና ማህበራዊ ስብዕናችው ከፍተኛ ብቃትና ተወዳዳሪነት ያላቸውን ምርጥ ወጣት ስፖርተኞች በማፍራት ሰልጣኞች ከስልጠናው ጎን ለጎን መደበኛ ትምህርታችውን እንዲከታተሉና ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ እንፃር ባለፉት ዓመታት ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ማዕከሉ ሰልጣኞችን በተለያዩ ውድድሮች በማሳተፍ እየተሰጠ ያለውን ስልጠና ለመገምገምና በውድደር ተሳትፎ የስልጣኞችን የተወዳዳሪነት ብቃታቸውን ያጎለብታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውድድር ተሳትፎ  ወቅት በተለያዩ ክለቦች እይታ እንዲያገኙ ዕድል በማመቻቸት በርካታ ሰልጣኞች በሚያሳዩት የተሻለ የውድድር ብቃት ሀገርን ወከለው በተለያዩ ውድድሮች ላይ ሊያሳትፋቸው በሚችለው ብሄራዊ ቡድን እንዲመረጡ ያደርጋል፡፡

በዚህ መሠረት የተለያዩ ሀገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች በሚዘጋጁት ፕሮግራምና በወዳጅነት ውድድሮች በየዓመቱ መሳተፍ ከመቻላቸውም ባሻገር በውድድር ተሳትፎ ላይ የሚገኙ ልምዶችን ለስልጠናው ሂደት በግብዓትነት መጠቀም ተችሏል፡፡

ይህ ተቋም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በተደረገው ጥረት 136 ሰልጣኞች ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ ሲሆን ከ540 በላይ ወደ ክለብ ተዛውረዋል፡፡

በአጠቃላይ በሀገራዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሰልጣኞችን በማሳተፍ ባስመዘገቡት ውጤት ተተኪነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡